Tuesday, May 10, 2016

የሙዝ ኬክ

የሚወስደው ግዜ:- አንድ ሰዓት ከአስር ደቂቃ (አስር ደቂቃ ዝግጅት፣ አንድ ሰዓት ማብሰል)
መጠን:- ለአስራ ሁለት ሰው የሚበቃ


2 ሙዝ
300 ግራም ስኳር
200 ግራም ቅቤ
2 እንቁላል
3 የሾርባ ማንኪያ ክሬም ከተገኘ
400 ግራም የፉርኖ ዱቄት
አንድ የሻይ ማንኪያ ቤኪንግ ሶዳ
አንድ የሻይ ማንኪያ ቫኒላ

በመጀመሪያ ኦቭኑን/ማብሰያውን 175 ዲግሪ ድረስ ማሞቅ።

ተለቅ ያለ ጎድጓዳ ሰሃን ውስጥ እንቁላሉንና ስኳሩን አብሮ መምታት። ቅቤውን ለስለስ ቀለጥ አድርጎ ወደ እንቁላሉ መጨመር። ሙዞቹን በሹካ በደምብ መፍጨትና ከክሬሙ ጋር ቀላቅሎ ከእንቁላሉ ጋር ማደባለቅ።

ዱቄቱና ቤኪንግ ሶዳውን ካቀላቀሉ በሗላ በአንድ ግዜ ሁለት የሾርባ ማንኪያ ያህል እያደረጉ ወደ ሊጡ መጨመርና በደምብ ማቀላቀል። ቫኒላ ካለ ጨምሮ ማደባለቅ::

ማብሰያውን ትሪ በቅቤ መቀባትና በተፈጨ የደረቅ ዳቦ ዱቄት መሸፈን። የትሪውን 2/3ኛ በሊጡ መሙላትና ወደሞቀው ማብሰያ አስገብቶ ለአንድ ሰዓት ያህል ማብሰል። የተለያዩ ማብሰያዎች የተለያይ ባህሪይ ስላላቸው የሚያስፈልገው ሙቀት ወይም የማብሰያው ግዜ ሊለያይ ይችላል። ኬኩ ከማብሰያው ሲወጣ በጥርስ እንጨት ወይም በተመሳሳይ ነገር ወጋ አድርጎ እንጨቱ ንፁህ ወይም ደረቅ ሆኖ ከወጣ ኬኩ በስሏል ማለት ነው። ኬኩን ለማሳመር ከፈለጉ በደቃቁ የተፈጨ ስኳር በማጥለያ ውስጥ በማሳለፍ መነስነስ። እንደፍላጎትዎ ኬኩን በሞቃትነቱ መይም አቀዝቅዘው መመገብ ይችላሉ።



Monday, March 21, 2016

ጥቁርና ነጭ


ክፍል አንድ


መልዕክት መቀበሌን የሚያበስረውን ፉጨት ሰማሁኝና ስልኬን ብድግ አደረኩኝ። 'ናፈቅሽኝ' ይላል። መልስ ሳልሰጥ ስልኩን አጠፋሁትና አጠገቤ ያለው ጠረዼዛ ላይ አስቀመጥኩት። አቅፎኝ የነበረውን እጁን ሰብሰብ ሲያደርግ ቀና ብዬ የጠቆረ ፊቱን ተመለከትኩና በረጅሙ ተነፈስኩኝ። የጠበኩት ንግግር ወድያውኑ ተጀመረ።

'ማርክ ማነው?'

'አንድ ጓደኛዬ ነው...ያለፈው ሳምንት አባቱ መሞታቸውን ነግሬህ ነበር'

ፀጥታ ሰፈነ። ሁለታችንም ቲቪው ላይ አፍጥጠናል። አስተነፋፈሱ ምን እያሰበ እንደሆነ ያሳብቅበታል።

'ለምንድነው በዚህ ሰአት መልዕክት የሚልክልሽ? ምንድነው ካንቺ የሚፈልገው?'

'አላውቅም ሚኪ... የሚያዋራው ሰው ፈልጎ ይሆናል'

እውነቴን ነው። ማርክ ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት መልዕክት ልኮልኝ አያውቅም። ሰሞኑን ከአባቱ ማረፍ በሗላ በስልክም በአካልም ተገናኝተን ብዙ ተጫውተናል። በሁለታችን መሃል ግን ከንፁህ ጓደኝነት ውጪ ምንም ነገር ኖሮ አያውቅም።

'እኔ ግን ለምን እንደዚህ እንደምታደርጊ በፍፁም አይገባኝም ሃኒ!' የደም ስሮቹ ግንባሩ ላይ ተገታትረው ወጥተዋል። 'ሁሉ ነገር ላንቺ ቀልድና ጨዋታ ነው... አንቺኮ ህጻን አይደለሽም...እንዳዋቂ ማሰብ ጀምሪ እንጂ!'

ደሜ ሲፈላ ይሰማኝ ጀመር። ምንድነው እኔ ያደረኩት ነገር? ማርክን እንደዚህ አይነት መልዕክት እንዲልክልኝ አላበረታታሁትም። እንደጓደኝነቴ በሃዘኑ ግዜ ከጎኑ ሆኜ ከማጽናናት ውጪ ያጠፋሁት ነገርም አይታየኝም።

'እንዴ! እኔ ምን እንድልህ ነው የምትፈልገው? እኔ የመልዕክቱ ተቀባይ እንጂ ላኪ አይደለሁኝም... ሌላ ሰው ላደረገው ነገር ደግሞ እኔን ተጠያቂ ልታደርገኝ አትችልም... ማርክ ፍቅረኛ እንዳለኝ ያውቃል። አንተ የምታስበውን ያስባል ብዬም አላምንም... ደግሞ ወዴት ነው የምትሄደው በዚህ ሰአት?'  ተነስቶ ጫማውን ማጥለቅ ጀምሯል።

'ወደቤት... ጠዋት ስራ መግባት አለብኝ'

ነገ እኮ ቅዳሜ ነው ልለው አሰብኩና ከአፌ ላይ መለስኩት። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። ሁሌም ጭቅጭቅ ሲነሳ የልቡን ከተናገረ በሗላ ያባረሩት ይመስል ሰበብ አስባብ ፈጥሮ ተሯርጦ ከአጠገቤ ይሸሻል። አሁንም ቀና ብሎ እንኳን በስርዓት ሳይመለከተኝ ደህና እደሪ አይነት ነገር አርጎምጉሞ ወጥቶ ሄደ።

እምባ ያቀረሩ አይኖቼን አደራረቁኝና ስልኬን አነሳሁኝ። ማርክ ምን ማለቱ ነው? ደጋግሜ ባነበው ግልፅ የሚሆንልኝ ይመስል ለብዙ ደቂቃዎች አፈጠጥኩብት። ማርክ ሚኪ እንደሚያስበው ከእኔ ሌላ ነገር ይፈልግ ይሆን? እኔስ እንደዚያ የሚያስብበት ምክንያት ሰጥቼው ይሆን? የማይመስል ነገር ማሰቤ አሳቀኝና ስልኬን መልሼ አስቀምጬ ከመተኛቴ በፊት ሰውነቴን ለመለቃለቅ ወደመታጠብያ ቤት አቀናሁ።

ተጣጥቤ ስወጣ ለሚኪ ደወልኩለት። እንዳሰብኩት ስልኩን አያነሳም። 'ይቅርታ ካጠፋሁኝ... ደህና እደር'  ብዬ መልዕክት ላኩለትና ወደመኝታዬ አመራሁ። 
ሰላምታ ለሁላችሁም


የመፃፍ ፍቅር አብሮኝ ያደገ ነው። በተለያየ ወቅትም አጫጭር ድርሰቶችን ለትቤትም ሆነ ራሴን ለማስደሰት ሞካክሪያለሁኝ። ትችት በመፍራት ግን እስካሁን ድረስ ድርሰቶቼን ለሰዎች አሳይቼ አላውቅም። በዚህ ረገድ ጥቁርና ነጭ የመጀመርያዬ ነው። እንደምትወዱት ተስፋ አደጋለሁ። እነሆ ክፍል አንድ፣ ቀጣዩ ክፍል ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት።


የእናንተው
ውቢት ኢትዮዽያ